Skip to main content
1234

ሆሳዕና የኢትዮጵያ ማንሰራራት አንዷ ማሳያ ናት - ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል። የኤፌዴሪ ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በወራት ውስጥ ገንብቶ በማጠናቀቅ ምሳሌ የሆነ ክልል ነው። 

ክልሉ በልማትም ሆነ በሰላም ረገድ ለሌላ አካባቢ ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን የቻለ መሆኑን ተናግረዋል። በሆሳዕና ከተማ የተሰሩ የልማት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ሚኒስትሯ ተናግረው፤ ከተማዋ የኢትዮጵያ ማንሰራራት አንዷ ማሳያ ናት ሲሉም ገልፀዋታል። በከተማዋ በአጭር ጊዜ የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና የትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች አመራሩ ከሕዝብ ጋር ያለውን ቅንጅት የሚያሳይ ነው ብለዋል። የተጀመሩ የልማትና ሰላምን የማፅናት ተግባራትን አመራሩ ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወ/ሮ እናትአለም መለሰ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለውጥ በተቀናጀና በተባበረ መንፈስ መሥራትን ይፈልጋል። 

ለውጥን ለማስቀጠል ሕዝብን በማሳተፍ መሥራት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ወጣቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማብቃት ተወዳዳሪና ብቁ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሕዝቡ ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት በሆሳዕና ከተማ በተከናወኑ ተግባራት ማሳየት ችሏልም ብለዋል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ፣ የከተማና ኢንዱስትሪ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል በበኩላቸው፤ የሕዝቡ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሽጉጤ ከከተማ ነዋሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ የመሠረተ ልማት በተለይም የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የመብራት ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላትም በሚቀርቡ አማራጮች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ አብዱልዋሲ አብዱላሂ (ዶ/ር) ፤ በወልቂጤ ከተማ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል። 

የወጣቱን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ህገ ወጥ ስደትን በአካባቢው ለማስቀረት በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። በከተማው የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከመደመር መንግሥት ጎን በመሆን እንደሚያስቀጥሉም አረጋግጠዋል። በዚህ ሂደት የመደመር መንግሥት ጥረትና ተነሳሽነት ከፍተኛ በመሆኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ሕዝቡ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በወልቂጤ ከተማ የነዋሪውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሆስፒታል ግንባታን ጨምሮ ሌሎችም የልማት ሥራዎች በጥራትና በፍጥነት በመጠናቀቃቸው አመስግነው፤ መሰል የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።